የአርሰናል ዋና አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ቡድናቸው በዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር ከባለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚችል በድፍረት ገልጸዋል።
“ጥሩ ነገር የመስራት ብቃቱ አለን” ሲሉ አስተያየት የሰጡት አርቴታ፣ “በእርግጠኝነት ትልቅ የተጨዋቾች ጥራት አለን፤ ይህንን ማረጋገጥ አለብን” ብለዋል።
መድፈኞቹ ባለፈው የውድድር ዘመን በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ከረጅም አመታት በኋላ እስከ ሩብ ፍጻሜ መድረሳቸው ይታወሳል። ይሁን እንጂ አሰልጣኙ ይህ እንኳን እንዳላረካቸው አስረድተዋል።
“ባለፈው አመት ለብዙ ጊዜ አስቸጋሪ ሆኖብን የነበረውን ሩብ ፍጻሜ አሳክተን ነበር። ነገር ግን ይህ አላረካንም። በዚህ አመት የበለጠ ነው የምንፈልገው” ሲሉ አርቴታ ጨምረው ተናግረዋል።
በመጪው የሻምፒየንስ ሊግ ጨዋታቸው ከአታላንታ ጋር እንደሚጋጩ የጠቆሙት አርቴታ፣ “ከአታላንታ ጋር መጫወት በጣም አስቸጋሪ ነው። የአሰልጣኝ ጋስፔሪኒ አድናቂ ነኝ፤ በአታላንታ እና በሌሎች ክለቦች ድንቅ ነገር ነው የሰሩት” ሲሉ ተናግረዋል።
አርሰናል በዚህ አመት በሻምፒየንስ ሊግ ምን ያህል እንደሚራመድ ለማየት የእግር ኳስ ወዳዶች በጉጉት ይጠባበቃሉ።